የ50ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ


የክቡር አባ አብርሃ ባራኪ የ50ኛ ዓመት የክብር ኢዮቤልዩ በዓል መታሰቢያ

‹‹የአባ አብርሃ ሕይወት ጉዞ ከየት እስከ የት?››

የክቡር አባ አብርሀ ባራኪ ስርወ-መሰረት ከኢሮብ እምብርት ይመዘዛል፡፡ ይህንን ማህበረሰብ የሚያስተሳስር አንድ ነገር አለ፡፡ ይኸውም በሕዝቡ ዘንድ የሰረፀው የማርያም ፍቅር በሁሉም ነገር ውስጥ እንዲያነሱዋት አድርጓቸዋል፡፡ አዛውንቱም፣ ጎልማሳውም፣ ወጣቱም፣ ህፃኑም ሁሉ የነገሮች ማሰሪያቸው፣ የእውነት መገለጫቸው፣ የፍቅር ትስስራቸው ‹‹ማሪያም ናት›› ዓሊተኒ ማሪያሞ!! ይላሉ ኢሮባዊያን - የአሊቴና ማርያም ድረሽልን እንደማለት ነው፡፡ የማርያም ፍቅር ከኢሮባዊያን ደም ጋር የተዋሀደ፣ ከኑሮዋቸው ጋር የተዛመደ በመሆኑ በሚገጥማቸው ችግርና መከራ በስሟ በርካቶች በአግባቡ ያልተተየበ ወይም ያልተፃፈ ግን ደግሞ ብዙ ተአምራትን አይቷል፡፡

በየወሩ 16 ለሁሉም ልዩ ቀን ናት፡፡ ይህችም ቀን ከሌሎች ቀናቶች በተለየ ‹‹ኪዳነ ምህረት›› የምህረት ኪዳን በመሆኗ ልዩ ስሜት ከማሳደሩም ባሻገር ልዩ ክብርና ትርጉም በሕብረተሰቡ አማኒያን ውስጥ የሚያሳድር ነው፡፡
ይህች ዕለት እናቶች በሐገር ባህል ልብስ አምረውና ተውበው ግርማ ሞገስ ተላብሰው እለቱን በድምቀት የሚቀበሉበት፣ በተለያየ ዝግጅቶች የሚያከብሩበት ነው፡፡ እዚህ ላይ ብዙ ተምሳሌቶች መኖራቸው የታወቀ ሆኖ፤ ለየት ባለመልኩ ወ/ሮ ሐጎሳ (የክቡር አባ አብርሃ ባራኪ እናት) እንደሌሎች ቀደምት እናቶች በወርሃ ግንቦት 1929 ዓ.ም ዕለተ ኪዳነ ምህረትን በዓል ለማክበር ዝግጅታቸውን አጠናቀው የዝግጅቱ ዕለትም እየቀረበ ሲመጣ በአቶ ባራኪ ወልደጊዮርጊስ ቤት ለቤቱ ድርብ የምስራች ይዞ ነበር ብቅ ያለው፡፡

ኢግዝአብሔር ወደዚህ ዓለም እንዲመጣ የፈቀደለት የዚህ ዓለም አዲሱ ‹‹ትንሽና ገና ጨቅላ ሕፃን›› ፍፁም ወሳኝና ልዩ የነበረ በመሆኑ እናቱና አባቱ ‹‹አብርሃ›› ብለው ሰየሙት፡፡ ከስሙ እንደምንረዳው የአካባቢያችን፣
የቤታችን ብርሃን ሆነ እኛም ተደሰትን ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን ማለት ነው፡፡

አባቶች ‹‹ስምን መልአክ ያወጣዋል›› ይላሉ፤ ሲተርቱም ‹‹ስም ይመርህ ሲተረጎምም ስም ይመራል›› ሲሉ …፤ ከሕይመታቸው ልምድ እግዚአብሔር ከገለፀላቸው አንድ የሆነ ስሜት ተነስተው ስለሆነ ወደፊትም መልሱን ይጠብቁታል፡፡ የአቶ ባራኪ ቤተሰብ ይህን የመጣውን ድንቅ፣ ልዩና እጅግ ወሳኝ የሆነ እንግዳቸው ከፍቅራቸውም ባሻገር ‹‹አብሪ ኮከብ›› እንዲሆንላቸው፣ የልባቸውን እግዚአብሔር እንዲመልስላቸው ‹‹አብርሃ›› ብለው፤ እደግልን፣ ተመንደግልን፣ ለእኛም ለአካባቢህም ብሎም ለሀገርህ አለኝታ፣ መከታ፣ መካሪ፣ ዘካሪ ያድርግህ ብለው መረቁት፡፡ ቀኑ 16 ወርሃ ግንቦት 1929፤ ልክ የታላቋ የኪዳነምህረት ቀን ነበረ፡፡

ይህ ጨቅላ በሁሉ ነገር የተካነ፣ ለሁሉ ነገሮች ትኩረት የሚሰጥ፣ ብልህና አስተዋይ እ/ርን ፈሪ እንዲሆንላቸው ተመኙ፡፡ እግ/ር የለመኑትን የማይነሳ፣ የነገሩትን የማይረሳ ድንቅ አምላክ በመሆኑ የቤተሰቡ ምኞትና ህልም ከቀን ወደ ቀን እውን እየሆነ በመምጣቱ ገና በ18 ዓመቱ ለአሁን ሕይወቱ መሰረት በመጣል ደረጃ በደረጃ ለመጓዝ ወደ ጎልዓ ኩዳሕናይ ንኡስ ዘርዓ-ክህነት መርቀው ሸኙት፣ በናፍቆት ተሰናበቱት … እሱም እንደዚያው ተሰናበታቸው፡፡ እዚያውም የ1ኛ ደረጃ ትምህርቱን ጨረሰ፡፡ በመቀጠል ወደ አዲግራት በመሄድ የ2ተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲግራት ከተማ አቢይ ዘርዓ-ክህነት አጠናቀቀ፡፡ ቀጥሎ በመጣው የእድሜ እርከን ወጣቱ አብርሃ ባራኪ ቀጣዩንና ወሳኙን የጉዞ መስመር መወሰን ነበረበት፡፡ መንገድን የሚመራ እ/ር በመሆኑ አብርሃ ባራኪ 3ት ዓመት የፍልስፍና 4ት ዓመት ደግሞ የነገረ-መለኮት ትምህርት በአዲግራት አጠናቀቀ፡፡

የሕይወት ጎዞ ብዙ መሰናክል የበዛበት በውጣውረድ የተሞላ በመሆኑ እየጨመርንና እያጎለበትን፣ እያሰፋንና ግራ ቀኝ መመልከት ባሰፋነው መጠን ውሳኔያችን እየከበደ፣ የሚረብሹ መንታ መንገዶች እየመጡብን መምጣቱ
ይታወቃል፡፡ ቀጣዩ የወጣት አብርሃ ባራኪ ውሳኔ የዛሬ 50 ዓመት፣ ለ50 አመት የማያወላዳ መሰረት ጥሎ የተደመደመ በመሆኑ እግ/ር በሁሉም ነገር የተመሰገነ ይሁን!!!

 ክቡር አቡነ አብርሃ ደስታ፣ ክቡራን ካህናት፣ ሲስተሮች፣ ክቡራን ምዕመናን እንዲሁም ደግሞ እጅጉን የተከበራችሁ የበዓሉ አስተባባሪዎች አዘጋጅ የሆናችሁ የባሌ ካቶሊካዊያን የአባ አብርሃ የመንፈስ ልጆች
የሆናችሁ አባቶች፣ እናቶች እና ወጣቶች … እንኳን ለዚች ቀንና ሰዓት በአንድ ላይ፤ በአንድ መንፈስ የክቡር አባ አብርሃ ባራኪ የ50 ዓመት የክብር ኢዮቤልዩ በአልን በዚህ በደመቀና ባማረ ሁኔታ ለማክበር እ/ር አበቃን፡፡ ‹‹ክቡር ያከብርሃል›› ብለው እንደሚተርቱት ሁሉ - ይህ በዓል በዚህ የቅዱሳን ማረፊያ በሆነው በመቂ ካቴድራል እንዲከበር የእግ/ር ፍቃዱ ቢሆንም ፅንሰ-ኃሳቡ ከመቂ ሀገረስብከት ጳጳስ ክቡር አቡነ አብርሃ ደስታ፣ ከባሌ የአባ አብርሃ ልጆች እንዲሁም ከሌሎች አባቶችና እናቶች የመጣ በመሆኑ ለሁላችሁም ክብር ይገባችኋል፡፡ ክቡር አባ አብርሃ ይህ የእርስዎ መልካምነትና የእ/ር ቸርነት የተገለጠበት በመሆኑ እንኳን በልጆችዎ ይህንን
ለማየት በቁ ለማለት እንወዳለን፡፡

 ከዚህ በመቀጠል የክቡር አባ አብርሃ ባራኪ የ50 ዓመት የክህነት ህይወት ጉዞ በዚች ሰዓት ለማቅረብ የማይቻልና እጅግ በርካታ በመሆኑ አጠር ባለ መልኩ ከብዙ በጥቂቱ አንኳር አንኳሩን ‹‹ወፍ በረር›› በሚባለው መልኩ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ ዓለም የምታሳየው ብዙ ገፅታዎች እንዳሏት ሁሉ የሰው ልጆችም ከእ/ር በተሰጣቸው ብዙ ድንቅ ተግባራትን ሲያደርጉ እናስተውላለን፡፡ የድንቅ ተግባር ጅምር ግን ‹‹ውሳኔ›› ነው!! ‹‹አቋም መውሰድና ዓላማ ማስቀመጥ›› ነው፡፡

ሚያዚያ 20/1960 ዓ.ም. ወጣቱ አብርሃ ባራኪ በማይነቃነቅ አቋም፣ ዓላማንና ግብን አስቀምጦ ክህነት የመቀበልን ውሳኔ የመአዘን ዲንጋይ ያኖረበት ዕለት ነው፡፡ ልክ በዚህ ቀን ወሳኙ ሰው በብፁዕ አቡነ ኃ/ማሪያም
ካሕሳይ እጅ ከሌሎች 3ት ጓደኞቹ ጋር የክህነት መዓረግን ተቀበሉ፡፡ ይህ የሆነው ልክ በ30 ዓመታቸው መሆኑ ነው፡፡

ከዚች ቀን በኋላ የመልከመልካም ወጣቱ አብርሃ ስምም ታሪክም ተቀየረ፤
- አብርሃ ወደ አባ አብርሃ፤ - እሱ ወደ እሳቸው ….. እኔም ከዚህ በመቀጠል አባ/ እሳቸው እያልኩኝ እንቀጥላለሁ፡፡

የአባ አብርሃ የመጀመሪያ ሀዋሪያዊ ስራ የተጀመረው በ1961 ሕፃን ሆነው ከቦረቁበት፣ ወጣት ሆነው ከዘለሉበትና ፍቅርን ካጣጣሙበት የትውልድ ቦታቸው ብዙም ባልራቀ በአዎ ቁምስና የክቡር አባ ሐጎስ ፍሱሕ
ረዳት በመሆን ነበረ፡፡ በዚህን ግዜ ምናልባት ከአዎ ተራሮች ቁልቁል እያማተሩ የተወለዱበት ቤታቸውን መመልከት በመቻላቸው ካሳለፉዋቸው የልጅነት ትዝታዎች እየተገናኙ እንደነበረ መገመት ይቻላል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም … አንዳንዴ ገና በአፍላ ወጣት ጉልበታቸው ሮጥ ሮጥ ብለው ወደ ደውሀን እየወረዱ የእናታቸውን ፍቅርና እንክብካቤ (ገንፎ በቅቤም ግዕዝምም እየቀረበላቸው) ደህና አድርገው አጣጥመዋል ብንል አልተሳሳትንም፡፡ እነዚህ ሁሉ መልካም አጋጣሚዎች ጉልበት የሆኑት አባ አብርሃ ባራኪ በአዎ ቁምስና ገና አንድ አመታቸውን እንኳን ሳያከብሩ በወርሀ ጥር 1961 ዓ.ም. ወደ ኣዲገራት ቤተ ጳጳስ  ትመለሱው  እስከ ሰኔ 1961 ክቆዩ በኃላ ፣በ1961 ወደ ዓሊቴና ቁምስና ተመድበው እስከ 1971 ዓ.ም.  የትምህርት ቤት አስተማሪና ዳይርክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡

አባ አብርሃ እውነት ወዳጅ፣ ታታሪ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ አንደበተ ርቱዕ፣ ሰው አክባሪ፣ ተማሪም ሆነ ማህበረ-ሰብ በአግባቡ እንዲቀረፅ ተግተው የሚሰሩ፣ በማስታረቅ ካልሆነ በማጣላት ተግባር የማይተባበሩ፣ ክህነትን
ከነሙሉ ባህሉ የተላበሱ እንደነበሩ እዛ ያወቁዋቸው ይናገሩላቸዋል - ይመሰክሩላቸዋል፡፡

በ1971 ዓ.ም. አባ አብርሃ የአባ ኪዳኔ ገብራይ ም/ዳይረክተር ሆነው በአዲግራት ንኡስ ዘርአ-ክህነት በመመደብ እስከ 1974 ዓ.ም. እዛው አገልግለዋል፡፡ ወርሐ ሐምሌ 1974 ዓ.ም. የአባ አብርሃ ባራኪ ሕይወት ወደ አዲስ ምዕራፍ የተሸጋገረበትና እምርታዊ ለውጥ የታየበት ነበረ፡፡ ይህም ከለመዱት ሕዝብና ቤተዘመድ እንዲሁም ማህበረ-ሰብ በመለየት ሚሲዮናዊ ባሕሪ ተላብሰው እንዲጓዙ በመፍቀድና በመፈለግ ይህንንም በቁርጠኝነት በተግባር የጀመሩበት ጊዜ ነው፡፡

አባ አብርሃ በወርሐ ሐምሌ 1974 እጅግ የተከበሩ አቡነ ስብሐትለአብ ወርቁ ከተከበሩ አቡነ ዮሐንስ ወ/ጊዮርጊስ ጋር በመስማማት ያቀረቡላቸውን ጥያቄ በመቀበል ፊደይ ዶኑም ‹‹Fidei Donum ›› ሆነው አሁን ወደ አሉበት በሰዓቱ መቂ ፕሪፈክት ተብሎ ሲታወቅ ወደ ነበረው ወደ አሁኑ የመቂ ቪካሪየት መጡ፡፡ አዲሱ የሕይወት አቅጣጫ ዳግም አባ አብርሃን ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ከአባታችን አቡነ ዮሐንስ ጋር ያጣመራቸው ነበረ፡፡ ከአዲግራት ተጉዘው መቂ በደረሱበት ሰዓት በፈገግታቸውና በትህትናቸው እንዲሁም በሰው አክባሪነታቸው፣ በተምሳሌትነታቸው በሚታወቁትና በሚዘከሩት እጅግ በተከበሩና በአይረሴው ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ወልደግዮርግስና በሌሎች በጊዜው በነበሩ በኮንሶላታና የክርስቲያን ወንድሞች፣ በኮምቦኒ ሲስተሮች የደመቀና ያማረ እጅግ ማራኪ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

ለሕብረተሰቡና ለማህበረሰባቸው ሊያበረክቱ የሚገባቸውን ግልጋሎት ከዚያች ቀን ጀምሮ በፍቅር ገቡበት፡፡ በየዋህነትና በብልጠት መሀል ብዙ መራራቅ ጥላቻም አለ፤ አባ አብርሃ አዲሱን ጉዞውን በየዋህ መንገድ ጀመሩት፡፡ በተፈጥሮዋቸው አርቀው ተመልካች፣ የዓላማና የተግባር ሰው በመሆናቸው እ/ር ብርታትና ጥንካሬ እየሆናቸው የሸዋና የደቡብ ምስራቅ ማለትም የባሌ ሐዋሪያዊ ተግባራቸውን በመቂ ካቴድራል ቆሞስ በመሆን ‹‹ሀ›› ብለው ጉዞዋቸውን ጀመሩ፡፡

እኝህ ፍቅርን ተላብሰው ፍቅር የሰጡት አባ አብርሃ በ7ት ዓመት የመቂ ጉዞዋቸው እጅግ ብዙና ቢዘረዘሩ የማያልቁ ሰብአዊና ሐዋሪያዊ ተግባሮችን መፈፀማቸውን ስገልፅላችሁና ስመሰክርላችሁ እጅግ በኩራት ነው፡፡ የመጀመሪያ ስራቸው የተጀመረው ብፁዕ አባታችን አቡነ ዮሐንስ አንደኛ ደረጃ በመስጠት የዘርዓ ካህናትና የአገር በቀል አገልጋይ የሴቶች ማዕከል፤ በኋላ የንፅሕት ማሪያም ልጆች ‹‹Doughters of Marry Emaculate›› ወደሚለው ያደገው ጎን ለጎን በአንድ ግዜ መሰራት አለበት ብለው በወሰኑት መሰረት የተጀመረውን የወንዶች ንኡስ ዘርዓ ክህነት መገንባት በመጀመር ነው፡፡ በኋላ ይህ ንኡስ ዘርአ-ክህነት ለአዋሳና ለሶዶ ሆሳዕናም ጭምር የትምህርትና የካህናት መፍለቂያ የአገልግሎት ማዕከል ሆኖ እንዳገለገለ እዚህ ላይ ልብ እንለዋለን፡፡

‹‹ብርሃንህ አበራ›› በሚል ስያሜ ለአባ አብርሃ የተሰጣቸው ስም የተገለፀበትና የታየበት ትርጓሜውም እውን በመሆን ከምንዚዜውም በላይ በአጭር ጊዜ ከዳር እስከ ዳር ደምቆና አምሮ የታየበት ነው፡፡ አባ አብርሃ የአዲስ ሕይወት፣ የአዲስ አቅጣጫ፣ የአዳዲስ ዝምድናዎችና የአዲስ ልምድ በሮችን በስፋት ከፍተው ለሁሉም እንዲዳረስ አደረጉ፡፡ 1981 ዓ.ም. በአባ አብርሃ ሕይወት ሌላ ውሳኔና አቋም የሚጠይቅ ሁኔታ ይዞ ብቅ ያለ የእድሜና የልምድ እርከን ነበረ፡፡ ብፁዕ አባታችን አቡነ ዮሐንስ ወ/ጊዮርግስ ሚሲዮናዊ ስራቸውን ‹‹የአገር ልጅ በአገር ልጅ በሚለው መርሀ መሰረት›› ወደ ባሌ ማስፋት እንደሚፈልጉና ለዛ ቦታ እንደመረጡዋቸው ሹክ አሏቸው፡፡ የባሌ ሚሲዮናዊ ስራ ሊከብድ እንደሚችል፣ ተግዳሮቶች በርካታ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቢገምቱም በድፍረታቸው የማይታሙት አባ አብርሃ የአቡነ ዮሐንስን ሐሳብ ከመደገፍ፣ ከማበረታታትና ከዛም አልፎ ተርፎ ከመቀበል ወደኋላ አላሉም፡፡

የባሌ ሚሲዮናዊ ስራ ይጀመር ዘንድ ታስቦ የነበረው እጅግ በተከበሩ በአባ ቦንዛኒኖ ከሚዘሪየር በተገኘው 4 ሚሊዮን ብር በተመደበለትና በኮንሶላታ አባቶች በአጋርፋ ሊሰራ ታስቦ በነበረው ሆስፒታል ነበረ፡፡ ይህ ይሳካ ዘንድ አቡነ ዮሐንስ፣ አባ አብርሃ፣ አባ ቦንዛኒኖና አባ ጳውሎስ አንገበን የተለያየ ጥረት አድርገው የነበረ ቢሆንም ሳይሳካ በመቅረቱ ፈንዱ ወደ ኬኒያ ዞረ፡፡

ከዚህ በኋላ አባ ጆን ዴማርክ አቡነ ዮሐንስን ወሳኝ የሆነ ምክር አካፈሉዋቸው ‹‹የማዘር ተሬዛ ሲስተሮች የትም ዓለም፤ በሶሻሊስት ዓለምም ሳይቀር ተቀባይነት ስላላቸው በነሱ በኩል ይሞከር›› የሚል፡፡ አቡነ ዮሐንስ በሰዓቱ የሶሻሊዝም አራማጅ የነበረውን የኮለኔል መንግስቱን ልብ በማለስለስና በማርገብ ተቀባይነት ሊገኝ የሚችለው አባ ዴማርክ በሰጡዋቸው ምክርና መንገድ መሆኑን በማመን ጥያቄያቸውን ለማዘር ተሬዛ አቀረቡ፤ ጥያቄያቸውም ተቀባይነት አገኘ፡፡ ማዘር ተሬዛም ወዲያው 3ት ሲስተሮች ወደ ባሌ ሮቤ አንዲመደቡ ወሰኑ፡፡

አባ አብርሃ በ1979 ወደ ሮቤ ለመጀመሪያ ጊዜ የሄዱት እነዚያን 3ት ስስተሮች ይዘው ነበረ፡፡ እዛ እንደደረሱ አባ አብርሃ በድንኳን ውስጥ፣ ሲስተሮቹ በአንድ ትንሽ ቤት ሰፈሩ፡፡ በንጋታው ለበሽተኞች ድንኳን ተከሉ፤ በሽተኞችንም የማሰብሰብ ስራ ተጀመረ፡፡ ይህ ቦታ የክርስቲያን በጎ አድራጎት ድርጅት ዳይረክተር በወቅቱ የነበሩት ወንድም ኦገስቲን ለማዘር ተሬዛ ሲስተሮች የሰጡዋቸው ነበረ፡፡

በ1979ዓ.ም. አባ አብርሃ ለአንድ ወር በየ 2ት ሳምንት ከመቂ እየተመላለሱ በቦታው ቀድመው ለነበሩት ምዕመናን እና ለሲስተሮች የቅዳሴ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይቷል፡፡

በ1980ዓ.ም. በባሌ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ታሪክ ገና ከጅምሩ ታላቅ እመርታ የታየበት ነበር፡፡ ይኸውም ብፁዕ አባታችን አቡነ ዮሐንስ ወልደጊዮርጊስ፣ ቅድስት ማዘር ተሬዛ፣ አባ ጆን ዴማርክና ሌሎች ሲስተሮች በአንድ
አውሮፕላን በባሌ አውሮፕላን ማረፊያ በክብር ደረሱ፡፡ የአውሮፕላን መምጣት በክብር ሲጠባበቁ የነበሩ የባሌ ዞን አስተዳደሮች፣ የመንግስት ባለስልጣኖች፣ የመስሪያቤት ሰራተኞችና ሕዝቡ በደማቅ ስነስርዓት ተቀበሏቸዋል፡፡ አባ አብርሃና በቦታው የነብሩ 3ቱ ሲሲተሮች ከሚቀበሉት መሀል በመሆናቸው የሕዝቡን የደስታ ስሜት እጥፍ ድርብ አድርጎት ነበር፡፡

በዚህ በተመሳሳይ ቀን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣኖች በተገኙበት ሁኔታ በጎባ በቅድስት ማዘር ተሬዛ ለሲስተሮች በተሰጠ ቦታ የመሰረት ድንጋይ ተጣለ፡፡ በ1980 ዓ.ም. ክቡር አባ ዘውዴ ኃይሉ ፤ ከአዲግራት ሰበካ ፊደይ ዶኑም ‹‹Fidei Donum>> ሆነው የነበሩ ካህን ለአንድ ሙሉ አመት በሮቤ በአንድ የኪራይ ቤት ውስጥ በመሆን ለሲስተሮች የቅዳሴ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይቷል፡፡

በ1981 ዓ.ም. አባ አብርሃ የመጀመሪያ መጨረሻ ሆኖ በድል የተጠናቀቀውን የባሌ ሚሲዮናዊና ሐዋሪያዊ ተልእኮ መሪ በመሆን ተመድበው ከሰፊው የባሌ ህዝብ ጋር ተቀላቀሉ፡፡ አባ አብርሃም ሐዋሪያዊ ስራቸውን
የጀመሩት ዶንሳ ተከራይተውት በነበረው ቤት ነው፡፡ ልክ ባሌ በገቡ በተመሳሳይ ዓመት፤ ሳይዘገዩ በ1981 አባ አብርሃ ወደ አካባቢው ባለስልጣናት ቀርበው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማንነት በማሳወቅና በማሳመን ቦታ እንዲሰጣቸው ጠየቁ፡፡ በዚህ መሰረት አሁን ያለውን ሰፊ ቦታ መርጠው ተቀበሉ፡፡

በዚህ ቦታ አሁን የምናያቸው በርካታ ስራዎች የሰሩ ሲሆን በተለይ በርካታ ሰዎችን በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሕግ መሰረት በመቅረፅ ከምእመናን ባሻገር ተምሳሌት የሆኑ ሰዎች ከቦታው እንዲገኙ አድርጓል ፤ እነ አባ ጎበዝ አየሁ፣
አባ አሸናፊ፣ አባ በለጠ፣ ሲስተር ሙላት፣ ሲስተር የሺ፣ ሲስተር መሰረት ሌሎችንም ….. በርካቶች አፍርቷል፡፡

የባሌ ሚሲዮናዊ ስራ በእግሩ እንዲቆም የማድረግ ስራ እንደዚህ በቀላል መታየት የሚችል አልነበረም - ቀላልም አልነበረም፤ ብዙ ተግዳሮቶች የነበሩበት፣ ብዙ ውጣ ውረድ የጠየቀ ገድል ነበረ፡፡ በአባ አብርሃ የ50 ዓመት ጉዞና የስራ ሕይወት ግርታ የበዛባቸው ወቅቶች - ጨለማን ያረገዙ ግዚያቶች በፊታቸው አልነበሩም ማለት አይቻልም፤ አባ አብርሃ ግን ጨለማ ላይ ብታፈጥ ያለ ሰዓቱ እንደማይነጋ የሚያውቁ - ይልቁንስ ፈጣርን ይዘህ ጨለማና መከራ ላይ ብታፈጥ ዋጋ እንዳለው የተገነዘቡ በመሆናቸው ከእ/ር ጋር አባ አብርሃ የሮጡትን ያክል ሰብስቧል!!! ለዚህም እግ/ር የተመሰገነ ይሁን!! እ/ር ቀሪ ሕይወታቸውንም ይባርክ!!

አባ አብርሃ የአዳባ ቤተክርስቲያን እንዲመሰረትም የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ ማለትም ቀድመው የድፕሎማሲ ስራ በመስራት መንገዱን ጠርገዋል፡፡ በዚህ መሰረት በጥቅምት 25/1992 ዓ.ም. አቡነ ዮሐንስ ወ/ጊዮርጊስ፣ አባ አብርሃ፣ ጌቱ በርሄና እኔው ራሴ ወደ አዳባ አመራን፡፡ ምሳችንን ዶዶላ ከመድረሳችን በፊት ባለው ወንዝ ዳር በልተን ጉዞዋችንን በመቀጠል አዳባ ገባን፡፡ አቡነ ዮሐንስ በደረስንበት ቦታ ሁሉ የተአምራታዊት ማሪያም ስካፕሌር በመሬት ውስጥ እየቀበሩ ቦታዎችን እየባረኩ ነበረ የሄዱት፡፡

በከተማ አስተዳደር አቶ ሀሰን ደፎና መሀንዲሱ አትክልት ምሩፅ ከሌሎች ጋር በመሆን ጥሩ አቀባበል አድርገውልን ካበቁ በኋላ የተለያዩ ቦታዎችን አስመረጡን፡፡ እኛ ግን በአንድ አፍ የአሁንን ቦታ መረጥን፡፡ የቦታ ርክክብ ስራ በ2 ወር ተጠናቆ ግንቦት 16/1992 የመዋዕለ ሕፃናት ግንባታ፣ በሰኔ 6/1992 ደግሞ የመጀመሪያ ቅዳሴ አሳረግን፡፡

 የአዳባ ሚሲዮንም ልክ እንደ ባሌ ሮቤ፤ እንደ በሁር ልጆቹ ስራውን የጀመረው በኪራይ ቤት ነበረ፡፡ ከብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ሕልፈተ ሕይወት በኋላ ክቡር አባ አብርሃ ባራኪ ቦታውን ከተረከቡት ከብፁዕ አባታችን አቡነ
አብርሃ ደስታ ጋር ልክ ከዛ በፊት ከአቡነ ዮሐንስ ጋር በነበራቸው ጥሩ መንፈስ ተቀራርበውና ተስማምተው በመመካከርና በመግባባት በመስራት ተጨማሪ ስኬቶች ያስመዘገቡ መሆናቸውን ስናስታውስ ኩራት እየተሰማን
ነው፡፡ ይህ የተመዘገበው ስኬት እንደ ከዚህ ቀደሙ የአብሮነት ውጤት በመሆኑ በዚህ አጋጣሚ ለአባታችን አቡነ አብርሃ ደስታ የላቀ ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን፡፡

ከበርካታ ስኬቶች መሀል በብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ወልደጊዮርጊስ ጌዜ ተጀምሮ በብፁዕ አቡነ አብርሃ ደስታ ጊዜ ፍፃሜውን ያገኘውና የተመረቀው የጎባ ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን ከብዙው መሀል መዘን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ብፁዕ አቡነ አብሃ ደስታ በሞራል፣ በምክር ከአባ አብርሃ ባራኪ ጎን በመቆም ለመንፈሳዊ ስራቸው ስኬት ተጨማሪና ዋነኛው ጉልበት ስለሆኑ በአባ አብርሃና በራሳችን ስም ልናመሰግንዎት አንፈልጋለን፡፡ እግዚአብሔር
አገልግሎትዎን ይባርክ!!

ከዚህ በተጨማሪ የ “De La Salle” ክርስቲያን ወንድሞች በሮቤ፣ በጎባ፣ በአዳባ፣ በአለም ገና፣ በሄረሮ፣ በቡቻ በብራዘር ኬቨን እና በብራዘር ቶማስ መሪነት ለሰሩዋቸው ስራዎች በዚህ አጋጣሚ ሳናመሰግን አናልፍም፡፡
ምክንያቱም በአካል በመሀላችን ባይኖሩም ለአባ አብርሃም ሆነ ለአጠቃላይ ቤተክርስቲያን በደማቁ በሚናገረው ስራቸው ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱና ቀጥታ የአባ አብርሃ የ50 ዓመት ጉዞ አካል በመሆናቸው ነው፡፡ በመጨረሻ “Not least but last” የባሌ ቤተክርስቲያን ራሱን ችሎ እንዲተዳደር በተወሰነው መሰረት ቦታውን ይዘው እያስተዳደሩና እየመሩ ለሚገኙ ለክቡር አባ አንጀሎ ‹‹የባሌ ሮቤ ሐዋሪያዊ አስተዳደር›› የቤተክርስቲያን ስራ
ቅብብሎሽ በመሆኑ የባሌ ሚሲዮናዊ ስራን ወደላቀ ደረጃ በሚያደርስ ጉልበት ፣ መንፈስና ጥበብ በመከወን ለአመርቂ ውጤት እንዲበቁ እግዚአብሔር ከጎናቸው እንዲቆም ያለንን ምኞት ከወዲሁ መግለፅ እንወዳለን፡፡

ስለዚህ ከዕለቱ የበዓሉ ባለቤት ሕይወት ጋር ቀጥታ የተቆራኙ በመሆናቸው በይሕወት ያሉትንም የሌሉትንም፡- ብፁዕ አቡነ ሐይለማሪያም፣ ብፁዕ አቡነ ስብሐትለአብ ወርቁ፣ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ወ/ጊዮርግስ፣ ብፁዕ አቡነ
አብርሃ ደስታ፣ አባ አንጀሎን እና ሌሎች እጅግ በርካቶች ካህናት፣ ስስተሮች፣ ቤተዘመድ፣ ምዕመናን ለአባ አብርሃ የክህነት ሕይወት መጎልበት ላደረጉት አስተዋፅኦ ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ ለዚህ በዓል መሳካት አስተዋፅኦ ላደረጉት በሙሉ በተለይም ብፁዕ አባታችን አቡነ አብርሃም ደስታ የመቂ ሐ/ስብከት ጳጳስ፣ ክቡር አባ ጎበዛየሁ ጌታቸው የመቂ ሐ/ስብከት የልማት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት
ሃላፊ እና የአቡኑ እንደራሴ፣ ክቡር አባ ሙላት ሰብሮ የመቂ ሐ/ስብከት ሐዋሪያዊ መምርያ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ ክቡር አባ ተስፋዩ ቢሻሞ የመቂ ኪዳነ ምህረት ቁምስና ቆሞስ እና ከቅርብም ከሩቅም የመጣችሁ የአባ አብርሃ ባራኪ ወዳጆችና ቤተሰቦች በዚህ ትልቅ አጋጣሚ ልዩ ምስጋና ማቅረብ እንወዳለን፡፡

የአባ አብርሃ የክህነት ጉዞ ደረጃ በደረጃ፤ ከአንደኛው ምዕራፍ ወደሌላኛው ምዕራፍ፣ ከአንደኛው እድገት ወደሌላኛው እድገት በመሸጋገር ይኸው 50 ዓመት አስቆጥሯል፡፡ ለዚህም ልዑል ቅዱስ ሕያው እ/ር የተመሰገነ ይሁን፡፡ በመጨረሻ ለክቡር አባ አብርሃ ባራኪ የዚህ ያማረ ትልቅ ታሪክ አካልም ባለቤትም እርሷ በመሆንዎ እንኳን ደስ አለዎት ማለት እንፈልጋለን፡፡ …………

ሁላችንም እዚህ ያለን እላይ በጠቃቀስነው መልኩ በረጅም ርቀት የተዘረጋው የአባ አብርሃ ባራኪ ዘመነ ክህነት እያማረና እየደመቀ እንዲሁም እየሰፋ 50 ዓመት የተጓዘበትን ሂደት በማሰብ እያከበርን ነው፡፡ ክቡር አቡነ አብርሃ ደስታ፣ ክቡራን ካህናትና ደናግል፣ የተከበራችሁ ምዕመናን ይህ ቀን እውን ሆኖ እዚህ በመሰብሰባችንና ይህንን በዓል ያማረና የደመቀ እንዲሆን በማድረግ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተባበራችሁ ሁላችሁንም ደግመን ደጋግመን ብናመሰግን የሚያንሳችሁ ካልሆነ የሚበዛባችሁ በፍፁም አይሆንም፡፡ ስለዚህ በድጋሚ እግ/ር ይስጣችሁ እንላለን፡፡

እግ/ር አምላክ ከሁላችን ጋር ይሁን!
ልዑል አምላክ መንገዳችንን ይባርክልን!!
እ/ር አምላክ አሻራችን ያረፈበትንም ሆነ እየሰራነው ያለ ስራችንን ለስኬት ያብቃልን!! ስላዳመጣችሁኝ
አመሰግናለሁ፡፡

ፀሐየ አለማ
መቂ
17/2/2011

No comments:

Post a Comment